በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና በመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን መካከል የመረጃ ልውውወጥ ትብብር መግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
የመግባቢያ ስምምነቱ የተዘጋጀው የመገናኛ ብዙሃን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ በመገናኛ ብዙሀን ህጎች አፈጻጸም፣ በመገናኛ ብዙሀን ባለቤትነት፣ የገንዘብ ምንጭ፣ የማስታወቂያና ስፖንሰር ገቢ ምንጭ፣ በመገናኛ ብዙሀን ስራ የሚሳተፉ የውጪ ሀገር ዜጎች እንቅስቃሴ፣ የበየነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት እና ሌሎች የትብብር መስኮች ላይ እንደ የተቋማቱ ሀላፊነት በትብብር ለመስራት እንዲቻል ነው፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ኢድሪስ በወቅቱ እንደተናገሩት የመገናኛ ብዙሃን ለአንድ ሀገር የዲሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ሚና ያለው ዘርፍ ነው፡፡ ይህንን ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ አክለውም ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጋር በጋራ መስራት የመገናኛ ብዙሀን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሃብት ህጋዊ አስመስሎ ለመጠቀም እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀል ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከማድረግ ባለፈ ተቋማቱ በጋራ መስራታቸው የመገናኛ ብዙሃን የፋይናንስ ደህንነትን በተመለከተ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማዳበር ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በበኩላቸው እንደተናገሩት የመገናኛ ብዙሃን ለአንድ ሀገር ዘርፈ ብዙ እድገት ያላቸው አዎንታዊ አስተዋጾ እንደተጠበቀ ሆኖ በህገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ለመጠቀም እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎች ማስፈጸሚነት እንዳይውሉ የተቋቋሙበትን አላማ፣ ባለቤትነት እና የፋይናንስ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህንንም ለማድረግ ተቋማቱ እንደተሰጣቸው ተልእኮ ወንጀሎቹን ከመከላከል አንጻር እርስ በእርስ መደጋገፍና የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ስምምነት መፈጸማቸው ትልቅ ደርሻ አለው ብለዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2014 መሰረት የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት የፋቃድ ሁኔታን የመወሰን፣ ፍቃድ የመስጠት፣ የመመዝገብና የማገድ ስልጣን ያለው ተቋም ሲሆን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በአዋጅ ቁጥር 780/2005 በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ/ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና መቆጣጠር መረጃ የመሰብሰብ፣ መተንተንና ማሰራጨት ሀላፊነት ያለው ተቋም ነው፡፡
0 Comments