ኢትዮጵያ በቀጠናዊ መድረክ እየተሳተፈች ነው
ኢትዮጵያ በ48ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጸረ-በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ መድረክ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡
በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ የተመራው ልዑክ በኬንያ እየተካሄደ በሚገኘው ቀጠናዊ መደበኛ መድረክ ላይ እየተሳተፈ ሲሆን በመድረኩ ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲሁም ከህግ አስከባሪ አካላት የፍትህ ሚኒስቴር የአቃቤ ህግ ዘርፍ እና የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ልዑካን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ቀጠናዊ ተቋሙን ለቀጣይ አንድ አመት በፕሬዝደንትነት ለመምራት ኢትዮጵያ በዚህ መድረክ ኃላፊነት እንደምትረከብ ይጠበቃል፡፡
የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጸረ-በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ቡድን (Eastern and Southern African Anti-Money Laundering Group-ESAAMLG) ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ/ንብረት ህጋዊ አስመስሎ መጠቀምን እና ሽብርተኝነትንና ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን ለመዋጋት የተቋቋመ ቀጠናዊ ተቋም ሲሆን 48ኛ መደበኛ ስብሰባውን በኬኒያ ዲያኒ ከተማ ከነሐሴ 17 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ያካሂዳል።
ቀጠናዊ ተቋሙ 21 አባል ሀገራት ማለትም አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ቡሩንዲ፣ ኤርትራ፣ ኢስዋቲኒ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ሌሶቶ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ሞሪሸስ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ስሸልስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ በአባልነት እንዲሁም ኮመንዌልዝ ሲክሬታሪያት፣ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ፣ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ-ሃይል፣ የዓለም ገንዘብ ተቋም (IMF)፣ የደቡባዊ አፍሪካ አገራት ልማት ማህበረሰብ (SADC)፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸረ-አደንዛዥ ዕፅ ቢሮ፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም ጉምሩክ ድርጅትን በታዛቢነት የያዘ ነው።
0 Comments