የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጸረ-ፋይናንስ ወንጀሎች ግብረ-ሃይል (ESAAMLAG) መደበኛ ጉባዔ በአሩሻ ታንዛኒያ በመካሄድ ላይ ይገኛል
ኢትዮጵያን ጨምሮ 21 አባል አገራትን ያቀፈው ቀጠናዊ የጸረ-በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሃብት ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ተቋም (Eastern and Southern Africa Anti-Money Laundering Group) 45ኛ መደበኛ ጉባኤ በታንዛኒያ አሩሻ እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 25 እስከ 31 በመካሄድ ላይ ይገኛል። በመድረኩ የአገራት የፋይናንስ ወንጀል መከላከል መደበኛ ክትትል ሪፖርት ቀርቦ በመገምገም ላይ ሲሆን አባል አገራት በአለም አቀፍ ስታንዳርዶች ተገምግመው ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ ውጤት ይፋ የሚደረግበት ነው።
በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሌን ጊዜወርቅ የተመራው እና የአገልገሎት መ/ቤቱ፣ የፍትህ ሚኒስቴር እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የስራ ኃላፊዎችን ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ሲሆን የአገራችንን 12ኛውን አገራዊ የወንጀል መከላከል አፈጻጸምና የክትትል (Follow up) ሪፖርት አቅርቦ አስገምግሟል።
ቀደም ሲል በተካሄደው የእርስ በእርስ መገማገሚያ (Mutual Evaluation) መድረክ ኢትዮጵያ የነበሩባትን ጉልህ የህግና ተቋማዊ ማዕቀፍ እንዲሁም የህግ አፈጻጸምና ውጤታማነት ጉድለት በሂደት በማሻሻል ከአርባ አለም አቀፍ ቴክኒካዊ መመዘኛዎች በሰላሳ ሰባቱ ላይ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቷን በመድረኩ ተገምግሞ ማረጋገጫ ተሰጥቷል። ቀሪ ሶስት መመዘኛዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶች በቀጣይ ተስተካክለው ሪፖርት እንዲቀርብ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ኢትዮጵያ አለም አቀፋዊ የፋይናንስ ደህንነት ስርዓት ለማረጋገጥ ደረጃዎችን በማውጣት፣ የአገራት አፈጻጸም በመከታተልና በመገምገም ውጤት የሚሰጠውን የፋይናንስ ድርጊት ግብረ-ሃይል (Financial Action Task Force) ቀጠናዊ ተቋም አባል በመሆን ጤናማና ከወንጀል መጠቀሚያነት የጸዳ የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት በመስራት ላይ ትገኛለች። በመሆኑም በአለም አቀፍ መስፈርቶች አተገባበር ጉልህ ክፍተት ካለባቸው አገሮች ዝርዝር በመውጣት ወደ መደበኛ ክትትል ከሚደረግባቸው አገሮች ዘርፍ በመካተት ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቷን በተቋሙ ግምገማ ተረጋግጦ አለም አቀፍ እውቅና የተሰጣት ሲሆን ቀሪ በግምገማ የተለዩ ጉድለቶችን ፈጥኖ በማስተካከል የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአባል አገራት ጋር በሁለትዮሽ መስራት የሚያስችል የቅንጅትና የትብብር መግባቢያ ስምምነቶች መፈረም ተችሏል፡፡
0 Comments