በአለምአቀፍ ንግድ ሽፋን ሀብት የማካበት፣ መሰወርና የማሸሽ ወንጀልን ለመቆጣጠር የቅድመ መከላከል ዘዴዎችን መከተል እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
አለምአቀፍ ንግድን ሽፋን ያደረገ በወንጀል ሀብት ማካበት፣ መሰወርና ከሀገር የማሸሽ ወንጀልን ለመቆጣጠር የቅድመ መከላከል ዘዴዎችን መከተል እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
አለምአቀፍ ንግድን ሽፋን ያደረገ በወንጀል ተግባር የተገኘ ሃብት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል አፈጻጸም እና የመከላከያ መንገዶቹ ላይ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ስልጠና የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ተሰጠ፡፡
አለምአቀፍ ንግድን መሰረት ያደረገ በወንጀል ተግባር የተገኘ ሃብት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ አለምአቀፍ የንግድ ልውውጥ ስርዓቶችን በመጠቀም ህገወጥ ሀብት ማካበት እንዲሁም በዚህም ሆነ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ ጥረት የሚደረግበት መንገድ ነው። ወንጀለኞች በህገወጥ መልኩ ሀብት ለማመንጨት እንዲሁም በወንጀል የተገኘን ሀብት ትክክለኛ ምንጩን ለመደበቅ ከሚጠቀሙባቸው አማራጮች መካከል አለም አቀፍ የንግድ ስርዓት አንዱ ነው። በዚህም ወንጀለኞች የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። በተለይም ትኩረት አድርገው ወንጀሉን የሚፈጽሙጽ የወጪ እና ገቢ ንግዱ ላይ ሲሆን በዚህም ወደ ውጪ የሚላኩ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች እና አገልግሎቶች ዋጋን እና ብዛትን በማሳሳት ወይም ሀሰተኛ የሽያጭና ግዥ መረጃ ማቅረብ በማቅረብ እና በማጭበርበር ህገወጥ ገንዘብ ለማግኘት እና ሀብትን ለመደበቅ ብሎም ህጋዊ ለማስመሰልና ከሀገር ለማሸሽ ጥረት ያደርጋሉ።
በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የሱፕርቪዥን እና ኮምፕሊያንስ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ተመስገን በስልጠናው ወቅት እንደተናገሩት ንግድን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚፈጸመው ወንጀል በአለም ላይ ከ2.5 ትሬሊዮን፣ ከአዳጊ ሀገራት 620 ቢሊዮን ዶላር፣ በኢትዮጵያ ከ1.2-3.1 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በየአመቱ ከዚህ ወንጀል እንደሚመነጭ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚጠቁሙ አመላክተዋል። አለምአቀፍ ንግድ ስርዓትን በመጠቀምም የመነጨውም ገንዘብ ህጋዊ መስሎ ወደ ህጋዊ የኢኮኖሚ ስርዓቱ ውስጥ ለማስገባት እንዲሁም በዚህ እና በሌሎች የወንጀል ተግባራት የተገኘ ሃብት ለመደበቅ እንዲቻል ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር እንዲሸሽ ይደረጋል ብለዋል።
ይህንን ለማድረግ በዋንኛነት ወንጀለኞቹ የሚጠቀሙበት ዘዴ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባን እና ከሀገር የሚወጣ እቃን ከትክክለኛው ዋጋው በማሳነስ ወይም በመጨመር፣ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባን ወይም የሚወጣን እቃ ከትክክለኛው ብዛት በመጨመር ወይም በመቀነስ በተጭበረበረ መልኩ ለተቆጣጣሪ አካላት በማሳወቅ ለእቃዎቹ ለመንግስት መከፍል ያለበትን ቀረጥ ባለመክፈል በገንዘቡ ህገወጥ ሀብት በማካበት እና በዚህ ተግባር እንዲሁም በሌሎች የወንጀል ተግባራት ያገኙትን ህገወጥ ሃብትን አለም አቀፍ የንግድ ስርዓትን በመጠቀም ወደ ውጪ ሀገር ለማሸሽ ጥረት ያደርጋሉ።
በወቅቱም እንደተገለጸው በዚህ መልኩ ሊፈጸም የሚችለውን ህገወጥ ሀብት የማካበት እንዲሁም የመሰወርና ከሀገር የማሸሽ ጥረት ለመከታተል እና ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ የቅድመ መከላከል ዘዴዎችን መከተል ያስፈልጋል። በዚህም ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስጋት ካለባቸው ሀገራት የሚኖር የንግድ እንቅስቃሴን በትኩረት መከታተል፣ ስጋት ያለባቸው እቃዎች በትኩረት መከታተል፣ ከእቃዎቹ ጋር የሚቀርቡ የደረሰኝና ሌሎች ሰነዶችን በትኩረት ማጣራት ያስፈልጋል።
የአለምአቀፍ ንግድን ስርዓትን መሰረት በማድረግ የሚፈጸመውን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሀብትን የማካበት እንዲሁም ከሀገር የማሸሽ ወይም የመሰወር ተግባር ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚመለከተቻው አካላት በጋራ በመሆን እየሰሩ ቢሆንም አሁንም ወንጀሉን በሚፈለገው ልክ መከላከል እንዳልተቻለ አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር በተያያዘ ሀገራዊ የመረጃ ቋት አለመኖር፣ የዋጋ ኢንዴክስ አለመኖር፣ በሀገርአቀፍ እና በአለምአቀፍ ደረጃ ከዚህ ጋር በተያያዘ የመረጃ መለዋወጫ ዘዴ የተሟላ አለመሆን እና በአሰራር ስርዓቱ ላይ ያለው ሙስና በዋንኛነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸው ተገልጿል።
አቶ ሙሉጌታ አክለው እንደተናገሩት በዚህ መልኩ የሚፈጸመውን ህገወጥ ሀብት የማካበት እንዲሁም በዚህ እና በሌሎች ህገወጥ ተግባራት የተገኘ ሀብት ለመሰወርና ከሀገር የማሸሽ ተግባርን መከላከል የሚቻለው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ ከሀገር የሚወጡ እቃዎችን በዋጋቸው ላይ በየጊዜው ያሉ ለውጦቹን እያሻሻለ መረጃ ማከማቸት የሚያስችል ሀገር አቀፍ የመረጃ ቋት መዘርጋትና ማጠናከር፣ ከአለምአቀፍ ንግድ ጋር በተያያዘ ያሉ የአሰራር ማእቀፎችን ማሻሻልና ግልጸኝነትን ማረጋገጥ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፍቃድ የሚሰጡና የቁጥጥር ስራ የሚያከናውኑ የመንግስት አካላትን ወቅቱን በማከለ መልኩ ያላቸውን እውቀትና ልምድ ማሻሻል እንዲሁም አጠቃላይ አሰራሩን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
0 Comments