በግብር ስወራ ወንጀል የሚመነጭ ገንዘብ ወደ ህጋዊ የኢኮኖሚ ስርዓቱ እንዳይገባና ተጠያቅነትን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳሚገባ ተገለጸ
በኢትዮጵያ የግብር ስርዓት፣ የግብር ስወራ ወንጀሎች፣ የግብር ስወራ እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ/ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎች ያላቸው ትስስር በተመለከተ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባለሙያዎችና በየደረጃው ላሉ አመራሮች ስልጠና የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ተሰጠ።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ የስልጠና መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት የግብር ጥሰት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል አመንጪ ወንጀል በመሆኑ በዚህ ወንጀል የሚገኘው ገንዘብ/ሃብት ወደ ህጋዊ ኢኮኖሚ እንዳይገባ ለመከላከል ብሎም ወደ ኢኮኖሚው ገብቶ ሲገኝ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በግብር ስርዓቱ እና በግብር ላይ ስለሚፈሙ ወንጀሎች የአገልግሎቱ ባለሙያዎች በየደረጃው ያሉ አመራሮች አስፈላጊውን ግንዛቤ የሚያገኙበት ስልጠና እንደሆነ ገልጸዋል።
ስልጠናው የተሰጠው በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገዙ ሲሆን ግብር መንግስት ለማህበረሰቡ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማከናወን እንዲችል ከግለሰቦች እና ከድርጅቶች የሚሰበሰብው ገንዘብ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ግዛትን እና ነዋሪነትን መሰረት ያደረገ የግብር አሰባሰብ ስርዓትን በመከተል ዜጎች ፍትሓዊ በሆነ መልኩ ከሚያገኙት ገቢ እና ከሌሎች የኢኮኖሚ ተግባራት ላይ ግብር የመክፈል ግዴታቸውን እንዲወጡ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
በስልጠናው ወቅት እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ከተለያዩ ገቢዎች ጋር በተያየዘ የምትከተለው የታክስ ስርዓት ሰንጠረዥን ማለትም የሚሰበስበው ግብር ከመቀጠር፣ ከቤት ኪራይ፣ ከንግድ ስራ ወዘተ ሆኖ ሁሉም የየራሱ የግብር መጠን ያለው መሆኑን ገልጸዋል። የታክስ አይነቶችን በተመለከተም ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ተብለው እንደሚከፈሉ ያብራሩት አቶ ሲሳይ የገቢ ግብር፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ተርን ኦቨር ታክስ፣ ኤክሳይስ ታክስ እና ሌሎች ላይም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ሲሳይ እንደተናገሩት አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎች የዜግነት ግዴታቸው የሆነውን ግብር የመክፈል ግዴታን ላለመወጣት የተለያዩ ህገወጥ ተግባራትን በማከናወን እንዲሁም በግብር ስርዓቱ ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ ክፍተቶችን ጭምር በመጠቀም ለመንግስት መከፈል ያለበትን ታክስ ለማስቀረት ጥረት ያደርጋሉ። በዚህም ያለ ደረሰኝ ሽያጭ ማከናወን፣ ለሽያጭ ሀሰተኛ ደረሰኝ ማቅረብ፣ ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ ማቅረብ፣ ህገወጥ የሆኑ ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ የንግድ ስምምነቶች ማከናወን፣ የእቃ ወይም አገልግሎት ትክክለኛ የዋጋ ትመና ባለማድረግ እና ሌሎች ጥሰቶችን በመፈጸም ሀገሪቷ ከግብር ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታጣ በማድረግ ኢኮኖሚው እንዲጎዳ ያደርጋሉ ብለዋል።
በስልጠናው ወቅት እንደተገለጸው ወንጀሎች የግብር ጥሰት ለመፈጸም የሂሳብ አዋቂ እና የህግ ባለሙያዎችን ጭምር የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ። በዚህ መልኩ የተገኘ ህገወጥ ሃብት ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወደ ኢኮኖሚ ስርዓቱ ውስጥ ለማስገባት ጥረትም ያደርጋሉ። የግብር ጥሰት/ስወራ ወንጀልን ለመከላከል የገቢዎች ሚኒስቴር የቁጥጥር እና የምርመራ ስራዎችን እንደሚያከናወን የገለጹት አቶ ሲሳይ በዚህ መልኩ የተጭበርበረን ከፍተኛ የሀገር ገቢን ማስመለስ የተቻለ ቢሆንም አሁንም በወንጀለኞች ምክንያት ሀገር እያጣች ያለው ሀብት በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በዚህ መልኩ የሚፈጸም ወንጀልን ለመከላከል መረጃን በአግባቡ በመያዝ እና የጥቆማ ስርዓትን በማጠናከር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አቶ ሲሳይ የተናገሩ ሲሆን አሁን እየተደረገ ካለው የቁጥጥር እና የክትትል ስራዎች በተጨማሪ ያለውን ወንጀል ለመቀነስ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን መገደብ እና ሌሎች የቁጥጥር ስርዓቶችን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። አክለውም የግብር ጥሰት/ስወራ የፈጸሙ ወንጀለኞች ያገኙትን ህገወጥ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚ ስርዓቱ ውስጥ በማስገባት ህጋዊ አስመስሎ እንዳያቀርቡ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከክልልና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የምርመራ ስራዎችን በማከናወን ህጋዊ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ አመላክተዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች እንደተናገሩት የግብር ጥሰት አንደኛው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ/ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል አመንጪ ወንጀሎች ውስጥ ግንባር ቀደም መሆኑ የሚጠቀስ ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የሚመነጭ ገንዘብ ወደ ህጋዊ ኢኮኖሚ ስርዓቱ ውስጥ እንዳይገባ እንዲሁም ተፈጽሞ ሲገኝም ሀብቱን ለማስመለስ አስፈላጊውን የፍተሻ፣ የማጣራትና ትንተና ስራ ለማከናወን እንዲቻል በተሰጠው ስልጠና ጠቃሚ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸው ወንጀሉን ለመግታት በጋር መስራትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
0 Comments