የ34 አገራት የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር የትብብር ፕሮግራም በኬንያ ናይኖቢ ይፋ ሆነ
በአውሮፓ ህብረት አስተባባሪነት የምስራቅ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሀገራት እና የመንን ጨምሮ 34 ሀገራትን በጋራ ያቀፈ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መረዳት ወንጀሎች እንዲሁም ምንጩ ያልታወቀ የገንዘብ እንቅስቃሴን የሚመለከቱ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጋራ ለመስራት የሚያግዝ ፕሮግራም በኬንያ ናይሮቢ በጥር ወር 2015 ዓ.ም ይፋ ተደርጓል።
ፕሮግራሙን ይፋ ለማድረግ በናይሮቢ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ከኢትዮጵያ ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ የተውጣጣ የልኡክ ቡድን ተሳታፊ ሆኗል።
የዚህ ፕሮግራም አጠቃላይ አላማ የተደራጁ ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎችን፣ የሽብር ተግባራትን እና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀጠናው ውስጥ ያሉ ሀገራት በአገር ውስጥ ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር እንዲሁም አገራቱ እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት ቀጠናዊና አለማቀፋዊ ትብብርን በማጠናከር ወንጀሎቹን የመከላከልና መቆጣጠር ውጤታማነት ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።
በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ ላይ በተደረገ ውይይት በምስራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ ቀጠና የሚገኙ ሀገራት እንዲሁም የመን ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጋራ ሰርተው ውጤት ሊያመጡባቸው በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ፣ ሀገራቱ በአለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ እየገቡ ባሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምክንያት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን፣ ለህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስቀድመው መከላከል በሚቻሉበት አግባብ፣ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአገራት መካከል የሚደረገውን ትብብር እንዲሁም በአገር ውስጥ በየአገራቱ የፋይናንስ ደህንነት ተቋማት፣ የፖሊስ ተቋማት እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት መካከል ትብብርና ቅንጅትን በማጠናከር ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉበት አግባብ ላይ ውይይት ተደርጓል።
ከዚህም በተጨማሪ ተሳታፊ ሀገራቱ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መረዳት ወንጀሎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባከናወነቻቸው ተግባራት ያላትን ልምድ አካፍላለች። በተለይም የአለም አቀፉ የፋይናንስ ደህንነት ተቋማት ህብረት የሆነው ኢግመንት ግሩፕ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ተቋም አባል ለመሆን ያከናወነቻቸው ተግባራት እንዲሁም ወንጀሎቹን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል ስትራቴጂያዊ ጉድለት ያለባቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ በአለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ ሀይል/ Financial Action Task Force/ ተካታ ከነበረችበት ዝርዝር ለመውጣት የወሰደቻቸውን እርምጃዎችን በሚመለከት የነበራትን ተሞክሮ ለሌሎቹ አጋርታለች።
የቀጠናው አገራትን የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ለመደገፍ ተከታታይ ተግባራት እንደሚከናወኑ ፕሮግራሙ ይፋ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል። በዚህ የትብብር ፕሮግራሙ ውስጥ የታቀፉ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ቦትስዋና፣ ሱዋቲኒ፣ አንጎላ፣ ኬንያ፣ ሌሴቶ፣ ማዳካስካር፣ ማላዊ፣ ሞሪሸስ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ሲሸልስ፣ ናሚቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ዙምባቤ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ካሜሮን፣ ኮንጎ፣ ጋቦን፣ ቻድ፣ ኮንጎ ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክን፣ ብሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ሳኦቶሜና ፕሪንስፔ ፣ ኮሞሮስ እና የመን ናቸው።
0 Comments