ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆነ በህገ-ወጥ መንገድ የተሰበሰበ የውጭ ምንዛሪ ታገደ
መንግስት በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ባንኮች በውጭ አገራት ገንዘብ የሂሳብ ደብተር የሚከፍቱበትን የዲያስፖራ አካውንት ህግና የአሠራር ስርዓት በመጣስ የተለያዩ ግለሰቦች በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባካሄደው ክትትል ማረጋገጥ ችሏል። በዚሁ መሠረት አገልግሎቱ እስካሁን ባደረገው ክትትል፣ የትንተናና ማጣራት ስራዎች 85 ግለሰቦች የተሰታፉበት እና መጠኑ 20,226,583 ዶላር (ሃያ ሚሊየን ሁለት መቶ ሃያ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሰማኒያ ሶስት ዶላር) የውጭ አገር ገንዘብ በባንክ እንዲታገድ በማድረግ ለወንጀል ምርመራ ተላልፏል።
ወንጀሉ የተፈፀመው የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችንና የማጭበርበር ስልቶችን በመጠቀም ሲሆን ከነዚህም መካከል አንደኛ ውጭ አገር ሳይሄዱ ውጭ አገር ሄደው የተመለሱ በማስመሰል ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በማቅረብና በመጠቀም፣ ሁለተኛ ከውጭ አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው በመግባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው እንደገቡ በማስመሰል ቀሪውን በህገ-ወጥ መንገድ ከጥቁር ገበያ ላይ በመሰብሰብና ሀሰተኛ ሰነድ/ዲክላራሲዮን በማቅረብ፣ ሶስተኛ የሌላውን ሰው ዲክላራሲዮን የራስ አስመስለው በመጠቀም፣ አራተኛ ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በተለያዩ ባንኮች የዲያስፖራ አካውንት በመክፈትና በመጠቀም በአጠቃላይ ሌሎች ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በመጠቀም የወንጀል ተግባራት መፈጸማቸውን መረዳት ተችሏል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባካሄደው ክትትል፣ ትንተናና ማጣራት ሂደት ውስጥ ግለሰቦቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዲያስፖራ አካውንትን በሚመለከት ያወጣውን መመሪያ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 እንዲሁም የወንጀል ህግን በመተላለፍ የተፈጠረውን ዕድል ለወንጀል መጠቀሚያ ማዋላቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
በመሆኑም በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊዎች ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጉዳዩ ለወንጀል ምርመራ የተላለፈ ሲሆን አገልግሎቱ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ በመሰል የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተገንዝበው ከድርጊቱ እንዲታቀቡ አገልግሎቱ በዚህ አጋጣሚ በጥብቅ ያሳስባል።
1 Comments