የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና የባንኮች የጋራ ምክክር መድረክ ተካሄደ
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና የባንኮች የጋራ ምክክር መድረክ ተካሄደ
________________________________
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በአገሪቱ ካሉ ባንኮች የውስጥ ቁጥጥርና ኮምፕሊየንስ አደረጃጀቶች ጋር አስቸኳይ የምክክር መድረክ አካሄደ።
በምክክር መድረኩ በአገራችን በተለያየ አግባብ ከተከፈቱ ጦርነቶች መካከል የኢኮኖሚ አሻጥሮችና ወንጀሎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ያብራሩት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የበላይ አመራሮች ወንጀሎቹን ለመከላከል ባንኮች ትልቅ ድርሻ ያላቸው በመሆናቸው በወቅታዊና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የተጠናከረ ስራ ማከናወንና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተነስቷል፡፡
በአገር ላይ የተከፈተው የፋይናንስ ወንጀልና የኢኮኖሚ አሻጥሩ ከፍተኛ ጉዳት የሚስከትል በመሆኑ እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ በድርጊቶቹ ውስጥ የሚሳተፉ አካላት የህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የፋይናንስ ተቋማት እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በህግ በተጣለባቸው ሃላፊነት መሰረት ተቀናጅቶ መስራት ግዴታ ያለባቸው መሆናቸው ተነስቶ ውይይት ተደርጓል። የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር ስራውን በሚመለከት ከባንኮቹ ኮምፕሊያንስ አደረጃጀቶች የተሳተፉት ኃላፊዎች በክፍተት መልክ በሚታዩና መሻሸል በሚገባቸው የህግና አሰራር ክፍተቶች ላይ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
በተጨማሪም ባንኮች ለተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎች ተጋላጭነት፣ በባንክ ውስጥ ባሉ አካላትና በእነዚህ አካላት ሽፋን የሚፈፀሙ የፋይናንስ ወንጀሎች መኖራቸውን በመድረኩ ተነስቷል፡፡ በተለይም ህጋዊ የፋይናንስ ግብይትና የባንክ ስርዓትን በመጠቀም ለጥቁር ገበያ የምንዛሬ ወንጀል መፈጸምና ለሌሎች ፋይናንስና ኢኮኖሚ ነክ ወንጀሎች መበራከት እንደ አንድ መንስኤ የባንኮች የውስጥ አሰራር ድክመትና ወንጀሉን ለመከላከል በህግ የተጣለባቸውን ግዴታ በተገቢው መጠን ባለመወጣታቸው ስለመሆኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ በሚካሄደው የተጠናከረ የህግ ማስከበር ስራ የባንክ ኃላፊዎችን ጨምሮ በየደረጃው በባንክ ውስጥ ያሉ አካላትን፣ ከባንክ ውጪ ያሉ የወንጀል ተሳታፊዎችንና ተዋናዮችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የጋራ መግባባት የተደረሰ ሲሆን ለወንጀሎች መፈጸም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የአሰራር ክፍተቶችና ብልሹ አካሄዶች ተበለው የተለዩትን በጋራ ለማስተካከል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 መሰረት በዋናነት የወንጀል መከላከል ሃላፊነት ያላቸው ተቋማት ናቸው። የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ደግሞ ወንጀሎቹን በሚመለከት መረጃ የመሰብሰብ፣ መተንተንና ማሰራጨት እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን የማስተባበርና ማቀናጀት ሃላፊነት የተሰጠው ነው።
0 Comments