አገልግሎቱ ከወንጀል ተግባር ጋር ግንኙነት ያላቸው የባንክ ሂሳቦችን አገደ
የኢፌዲሪ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከህገ-ወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 665 (ስድስት መቶ ስልሳ አምስት) የባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ አገደ።
በአገልግሎቱ የታገዱት የባንክ ሂሳቦቹ ህጋዊ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ፈቃድ ሳይኖራቸው በህገ-ወጥ መንገድ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ከሉ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር በህገ-ወጥ መንገድ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሲሆኑ በወንጀል ድርጊቶቹ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተጠናከረ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።
የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም የተገኘን ሃብት ከህጋዊ ምንጭና በህጋዊ መንገድ የተገኘ በማስመሰል የመጠቀም ወንጀሎች አፈፃፀም በየጊዜው እየተቀያየረ ያለ ወንጀል ከመሆኑም ባሻገር ከወንጀል ድርጊቶቹ የተገኘው ሃብት ሽብርተኝነትን በገንዘብ ለመርዳት ወንጀል መፈፀሚያ ጭምር የሚውል በመሆኑ የመከላከልና መቆጣጠር ስራው በተጠናከረ አግባብ በመከናወን ላይ ይገኛል።
ስለሆነም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርገው ሂደት ህብረተሰቡ መረጃና ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ያቀርባል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት
መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም
0 Comments