በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ ማከናወን ትኩረት እንደሚሰጠው ተገለጸ
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አመራር እና ሰራተኞች በ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና በ2015 እቅድ ላይ አመታዊ የውይይት መድረክ ነሀሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም አካሂደዋል።
በወቅቱም የተቋሙ የ2014 እቅድ አፈጻጸም እና የ2015 እቅድ ለተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል። በቀረበው ገለጻም ተቋሙ በ2014 በጀት ዓመት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ ሽብርተኝነትንና ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሀገር ውስጥ ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር እና ከአለም አቀፍ አጋር ተቋማት ጋር በመሆን በርካታ ተግባራት መከናወናቸው ተገልጧል። በዚህም ከሪፖርት አቅራቢ ተቋማት ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው በሚችሉ አጠራጣሪ ግብይቶች ላይ ፍተሻና ትንተና በማከናወን ለተጨማሪ ምርመራ ለሚመለከታቸው ህግ አስከባሪ አካላት መተላለፉ፣ ወንጀሎቹን የመከላከል ኃላፊነት የተጣለባቸው በርካታ ተቋማት ላይ የሱፐርቪዥንና ቁጥጥር ስራ መከናወኑን፣ ከሀገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት እና ከሌሎች ሀገራት መሰል ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት የሚያስችሉ የትብብር ስምምነቶች መፈጸማቸውን፣ ወንጀሉን ለመከላከል የህብረተሰቡንና የባለድርሻ አካለትን ግንዛቤ ለማሻሻል ልዩ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸው ከአፈጻጸሞቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በ2015 በጀት አመትም ከሪፖርት አቅራቢ ተቋማት እንደዚሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ያለውን የመረጃ ቅብብሎሽ በኦንላይን ስርዓት እንዲፈፀም ማድረግ፣ ወንጀሎቹን ለመከላከል እንዲቻል የስጋት ተጋላጭነት ጥናቶችን ማከናወንና መተግበር፣ የቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር እና የህብረተሰቡን እና የባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መሻሻል እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ዋና ዋና እቅዶች መሆናቸው ተገልጧል።
ከቀረበው ሪፖርት እና እቅድ መነሻነት በርካታ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከዚሁ ጋር በተያየዘ ወንጀሎቹ ከመፈጸማቸው በፊት ለመከላከል ከተለያዩ አካላት የሚሰባሰቡ መረጃዎች ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን የማድረግ፣ ከክልሎች ጋር ስላለው ቅንጅታዊ ስራ፣ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና አጋር አካላት ጋር መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች፣ ከሰራተኛ የመፈጸም አቅም ግንባታ ጋር በተያያዘ እና ሌሎች ሀሳብ እና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሀሚድ አብዱልወሃብ በወቅቱ እንደተናገሩት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀልን በተመለከተ እንደሀገር ያለው ግንዛቤ አሁንም አነስተኛ በመሆኑ የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ እንዲሁም የተቋሙ ባለሙያዎች ተቋሙ የተሰጠውን ተግባርና ሀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሌን ጊዜወርቅ እንደተናገሩት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ከበርካታ ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸው በስምምነቱ መሰረት ቅንጅታዊ ስራዎችን ለማጠናከር ለማድረግ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል። ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከክልሎች በጋራ ለመስራት ቋሚ የሆነ እና ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ አባላት የሚኖርበት ፎረም እንደሚቋቋም እና ወደ ተግባር እንደሚገባም ገልፀዋል። አክለውም የተቋሙን 2015 በጀት ዓመት እቅድን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የተቋሙ አመራርና ሰራተኛ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት በላቀ እንዲወጣ አሳስበዋል።
0 Comments