ባለድርሻ ተቋማት በስራቸው ሂደት አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲመለከቱ ጥቆማ መስጠት እንዳለባቸው ተገለጸ
በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎችን አስመልክቶ ከፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ አገልግሎት፣ ከአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት እና ከዲ.ኤች.ኤል የፖስታ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ለተወጣጡ ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እንደገና ለማቋቋሚያ በወጣው አዋጅ ቁጥር 490/2014 ላይ ተቋሙ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል የህብረተሰቡን እና የባለድርሻ አካላትን በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎችን አስመልክቶ ያላቸውን ግንዛቤ ማጎልበት አንዱ በመሆኑ እና እነዚህ ተቋማትም በህግ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት ለህብረተሰቡ በሚሰጧቸው አገልግሎቶች ላይ ከእነዚህ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ተግባራትን ሲመለከቱ አስፈላጊውን መረጃ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጥቆማ መስጠት እንዲችሉ ግንዛቤ ማስጨበጥ አስፈላጊ በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
በወቅቱም በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎች ጽንሰ ሀሳብ፣ ስለወንጀሎቹ አፈጻጸም፣ በሀገር ላይ ስለሚያደርሱት ዘርፈ ብዙ ጉዳት፣ በወንጀሎቹ ዙርያ ያሉ አለምአቀፍ እና ሀገር አቀፍ የህግ ማእቀፎች፣ ወንጀሎቹን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ስለሚኖራቸው ድርሻ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም ስለቨርቹዋል ገንዘብ ግብይት እና በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎች ጋር ስላለው ግንኙነት የተዘጋጁ ሰነዶች ለተሳታፊዎች ቀርበው ገለጻ ተደርጎባቸዋል፡፡
ወንጀለኞች በህገወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ/ንበረት ህጋዊ አስመስለው ለመጠቀም ወደ ፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እና መሰል ተቋማት የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ይዘው በመቅረብ ሀብቱን ህጋዊ አስመስለው ለመጠቀም፣ ለማስመዝገብ እንደዚሁም ለሌላ ለማስተላለፍ የተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ስለሚችሉ በዚህ ጉዳይ ላይ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲገጥማቸው ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጥቆማ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በተመሳሳይ የፖስታ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 ላይ በፋይናንስ ተቋምነት ከሚፈረጁ ተቋማት መካከል የሚገኙ በመሆኑ ከወንጀሎቹ ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲገጥማቸው ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ተገንዝበው በወንጀሎቹ አፈጻጸም ዙርያ እና ስለሚያስከተሉት ጉዳት ተረድተው ወንጀሎቹን ለመከላከልና መቆጣጠር የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው በስልጠናው ወቅት ተገልጿል፡፡
ከተቋማቱ የተወጣጡት የስልጠናው ተሳታፊዎች እንደገለጹት በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎች መከላከልና መቆጣጠር የሚቻለው በአንድ ተቋም ብቻ በሚያከናውነው ተግባር ባለመሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ህብረተሰቡ በጋራ መስራት ሲቻል እንደሆነ እና በወንጀሎቹ አፈጻፃም ዙርያና ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ በሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ደህንነት ላይ ሊያደርሰው ስለሚችለው አሉታዊ ተፅእኖ በተሰጠው ስልጠና በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ተቋማቸው በህግ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት ለህብረተሰቡ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ከእነዚህ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥማቸው ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጥቆማ እንደሚልኩ እንደዚሁም በስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች ባልደረቦቻቸው እንደሚያጋሩ ተናግረዋል፡፡
0 Comments