ፋይናንስና ኢኮኖሚ ወንጀሎች መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ መድረክ ተካሄደ
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ከፍተኛ አመራሮች ጋር መጋቢት 02 እና 03 ቀን 2014 ዓ.ም የስልጠናና ምክክር መድረክ አካሄዳ።
በስልጠናና ምክክር መድረኩ ላይ የፋይናንስ ወንጀሎች ምርመራ፣ የታክስ ማጭርበር ወንጀል ምርመራ፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የቨርቹዋል ገንዘብና ተያያዥ ወንጀሎች እንዲሁም ወንጀሎቹን በመከላከልና መቆጣጠር በሚመለከት በባለድርሻ አካላት የትብብርና ቅንጅት ሁኔታ ላይ ሰፋ ያለ ውይይትና ምክክር ተደርጓል።
የፋይናንስ ወንጀሎች ምርመራን አስመልክተው ስልጠና የሰጡት አቶ ሙሉጌታ ተመስገን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈፀም የተገኘን ገንዘብ/ንብረት በትክክለኛው መንገድ የመጣ ሃብት ለማስመሰል ልዩ ልዩ የመደበቂያና ማስመሰያ ሂደቶች እንደሚፈፀሙ አብራርተዋል። የታክስ ማጭበርበር ወንጀል አንዱ የወንጀሉ ምንጭ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሙሉጌታ የፋይናንስ እንዲሁም የታክስ ወንጀል ምርመራ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የቨርቹዋል ገንዘብን አስመልክቶ ስልጠና የሰጡት አቶ ዮናስ ማሞ በኢትዮጵያ ህጋዊ የመገበያየ ገንዘብ የኢትዮጵያ ብር ብቻ ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦች የቨርቹዋል ገንዘብን አስመልክተው በሆቴል ውስጥ፣ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችና በተለያየ መንገድ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል። የቨርቹዋል ገንዘብ በየትኛውም አገር እውቅና ያልተሰጠውና ባለቤቱ የማይታወቅ ነው ያሉት አቶ ዮናስ ከኢትዮጵያ የቨርቹዋል ገንዘቡን የሚገዙት በዶላርና መሰል የውጭ አገራት ገንዘብ በመሆኑ ጉዳዩ ከወንጀል ጋር እንደሚገናኝም አስረድተዋል።
ከህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተያየዘ በርካታ ተሳታፊዎችን ያከታተ የወንጀል አፈፃፀም ሰንሰለት መኖሩን ያመላከቱት አቶ ዮናስ እነዚሀም ደላሎች፣ አስመጪና ላኪዎች፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎች እንዲሁም አልፎ አልፎ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ የፋይናንስ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉበት አብራርተዋል።
የስልጠና ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው ከቨርቹዋል ገንዘብ ጋር በተያየዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እስካሁን በቂ ትኩረት ያልተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰው ይህም ከግንዛቤ ጋር እንደሚገናኝና በቀጣይ በአንክሮ መታየት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎቹ በአጠቃላይ ከስልጠናው ጠቃሚ ግብዓቶችን ማግኘታቸውን ጠቅሰው በፋናንስና ኢኮኖሚ ረገድ የሚፈፀሙ በርካታ ወንጀሎች በመሆናቸው ወንጀሎቹን ለመከላከልና መቆጣጠር በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የተፈጠረውን ተቋማዊ አቅምና ዕድል የበለጠ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልፀው ከአገልግሎቱ ጋር የተለያዩ የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች መከናወናቸውን በቀጣይም ያለውን የስራ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንሚገባ አመላክተዋል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሃሚድ መሀመድ አገልግሎቱ ውስጣዊ አቅሙን ይበልጥ የማጠናከር ስራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው ከፌዴራል ፖሊስ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ያለው የስራ ግንኙነት በተሻለ የማጠናከር ስራ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚከናወንም ገልፀዋል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት እንዲሁም የፋይናንስና ኢኮኖሚ ወንጀሎችን በሚመለከት መረጃ የመሰብሰብ፣ መተንተንና ማሰራጨት እንዲሁም የኦፕሬሽን ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር የማከናወን ብሎም ባለድርሻ አካላትን በአገር አቀፍ ደረጃ የማስተባበር ኃላፊነት አለበት።
0 Comments