በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት መካከል የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነ - ስርዓት ተካሄደ
በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና በፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት መካከል በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሁለቱ ተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥ ለማድረግና በትብብር ለመስራት እንዲቻል የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ - ስርዓት የካቲት 28 ቀን 2014 ተካሄደ።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ በወቅቱ እንደተናገሩት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል የመረጃ ቅብብል ለማድረግ ከዚህ ቀደም ስምምነት ተደርጎ በጋራ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው የአሁኑ ስምምነት ከዚህ በፊት የነበረውን የማንዋል የመረጃ ቅብብሎሽን ወደ ሲስተም የሚቀይር ሲሆን ይህም በወንጀሎቹ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መረጃ ተቋሙ በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ባለስልጣን ዳታ-ቤዝ ላይ በቀጥታ በመግባት መረጃ ማግኘት ያስችላል ብለዋል። ከዚህም የሚገኘው መረጃ ተቋሙ የወንጀል ድርጊቶችን ከመነሻቸው ለመመርመር የሚያደርገውን ጥረት ከመደገፍ አንጻር ትልቅ አስተዋጾ አለው ብለዋል።
የኢፌዲሪ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ መሉቀን አማራ በበኩላቸው እንደተናገሩት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተቋማቱ መካከል የመረጃ ቅብብሎሽ ለማድረግ በተደረገው ስምምነት መሰረት በትብብር መንፈስ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሆኑ ገልጸው በወረቀት (በማንዋል) የነበረውን የመረጃ ቅብብሎሽ በሲስተም እና ኦንላይን እንዲደገፍ በማድረግ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀሎቹ የተጠረጠሩ አካላትን መረጃ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዳታ-ቤዝ በቀጥታ በማግኘት መረጃዎችን እንዲያገኝ መደረጉ ተቋማቱ ወንጀሎቹን ከመከላከል አንጻር በበለጠ በቅንጅት እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል። አክለውም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ወንጀልን የመከላከል ተግባር በአንድ ተቋም ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ አገልግሎትን ጨምሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ተነሳሽነት በመፈጠሩ ምስጋና አቅርበው ለሌሎች ተቋማትም አርያ እንደሚሆንም ጨምረው ገልጸዋል።
0 Comments