በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ በማስመሰል የሚጠቀሙ እና የሽብር ተግባርን በገንዘብ የሚደግፉ አካላትን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሶፍትዌር ተዘጋጀ
በሶፍትዌሩ አጠቃቀም ላይ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር /ኢንሳ/ ጋር በመተባበር በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ በማስመሰል የሚጠቀሙ እንዲሁም የሽብር ተግባርን በገንዘብ የሚደግፉ ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ ሶፍትዌር አዘጋጀ፡፡
በአደጉ አገራት ኤ.ኤም.ኤል. ሶፍትዌር (Anti money laundering software) በሚል የሚታወቀው መሰል ሶፍትዌሩ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ የማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀልን ለመከታተልና ለመቆጣጠር በስፋት ስራ ላይ የሚውል ነው። በሀገራችን ባለሙያዎች የበለጸገው አዲሱ ኤ.ኤም.ኤል ሶፍትዌር የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ወንጀሎቹን ለመከታተልና ለመቆጣጠር እየተጠቀመበት የነበረውን ነባር የትንተና ሲስተም በብዙ መልኩ ያሻሻለ ነው፡፡
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢንተለጀንስ ሲስተም ቡድን መሪ እና የዚህ ሶፍትዌር ሲስተም ማበልጸግ ፕሮጀክት ቴክኒካል ማናጀር አቶ ኪሩቤል ወንድአፍራው እንደተናገሩት የሶፍትዌር ሲስተሙን ለማበልጸግ ለሰባት አመታት ሲሰራበት እንደነበረ ጠቅሰው ሲስተሙም አለምአቀፍ ተሞክሮዎችን መሰረት ያደረገ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተ እና ከውስን የሰዎች ጣልቃ ገብነት በስተቀር ከተለያዩ ምንጮች ወደ ሲስተሙ የሚገቡ መረጃዎችን በራሱ የሚተንተን እና የኢንተለጀንስ ስራ የሚያከናውን ነው ብለዋል፡፡
አክለውም እንደ ገለጹት ወደ ትግበራ ለመግባት የተዘጋጀው ይህ ኤ. ኤም. ኤል(AML) ሶፍትዌር በዋናነት ሁለት ንኡስ ሲስተሞችን ያካተተ ሲሆን አንደኛው በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ የማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎችን በተመለከተ የፋይናንስ ተቋማት አጠራጣሪ ግብይቶች ሪፖርት ለፋይናንስ ደህንነት አገልገሎት የሚልኩበት ሲሆን ሌላኛው ንኡስ ሲስተም የተላከው ሪፖርት ላይ የትንተና እና የኢንተለጀንስ ስራ የሚሰራ ነው፡፡
በፋይናንሰ ደህንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ፍተሸና ትንተና ቡድን መሪ አቶ ዮናስ ማሞ እንደተናገሩት ይህ ሶፍትዌር በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ የማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎች ላይ የተቀናጀ ክትትል እና ቁጥጥር ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡ ሲስተሙም በተቋሙ በየደረጃው ላሉ ሰራተኞች ወንጀሎቹን በተመለከተ በሚመለከታቸው አካላት በሚቀርቡ ሪፖርቶች መሰረት የትንተና ስራ ለማከናወን እንዲሁም የክትትል እና የቁጥጥር ስራ ለማከናወን የተለያዩ ሚናዎችን የሚሰጥ በመሆኑ የተቋሙ ሰራተኞ ተቀናጅተው መስራትን ያጠናክራል ብለዋል፡፡ እንደዚሁም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ጋር በተያያዘ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ በርካታ ግለሰቦች ተሳታፊ ሊሆኑ ስለሚችሉ ሶፍትዌሩ በወንጀሉ የተሳተፉ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን በፋይናንስ ስርዓቱ ውስጥ ያላቸውን የቀድሞ ታሪክ መለየት የሚያስችል በመሆኑ የወንጀሉን ዋና አቀነባባሪ ግለሰብ ወይም ድርጅት በመለየት ክትትል እና ቁጥጥር ለማድረግ እንደሚያስችልም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አቶ ዮናስ አክለው እንደተናገሩት በሀገራችን ካሉ በርካታ የፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም ከህብረተሰቡ ወንጀሎቹን በተመለከተ የሚቀርቡ አጠራጣሪ ሪፖርቶችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ እና ወንጀለኞችም በርካታ የማስመሰያ እና የመደበቂያ ስለቶችን እየተጠቀሙ በመሆኑ ይህ የሶፍትዌር ሲስተም በልጽጎ ወደ ተግባር ለመግባት መዘጋጀቱ ወቅቱን የጠበቀ እና ወንጀሎቹን ከመከላከል አንጻር የተቋሙን አቅም በእጅጉ የሚያሳድግ ነው ብለዋል፡፡
0 Comments