በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና በፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና በፌደራል ዋና ኦዲተር መካከል በትብብር እና በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ተፈረመ።
የመግባቢያ ስምምነቱ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብን ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነት በገንዘብ የመደገፍን ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና በፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መካከል የመረጃ ልውውጥ ለማድረግና በትብብር ለመስራት ነው፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ተቋማቸው በተሰጠው ስልጣን እና ተግባር መሰረት በዋነኛነት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎችን መከላከል ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ተቋሙ ብቻውን ማከናወን ስለማይችል ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ሀገራት ተቋማት ጋር በትብብር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል ትላልቅ ሀገራዊ ግዢዎች በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስቀድሞ ለማከላከል ከፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጋር ወጥ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
የዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው እንደተናገሩት ይህ ስምምነት መደረጉ የዋና ኦዲተር መ/ቤት የፌደራል መንግስት ገንዘብንና ንብረት በወጡት ህጎች መሰረት መጠበቁን እና በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን ኦዲት በማድረግ ተግባሩ ላይ የሚገኙ ወንጀል ነክ ግኝቶችን ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ሪፖርት በማድረግ ወንጀሉ ስር ሳይሰድ ክትትል እንዲደረግበት ለማድረግ ያስችለል ብለዋል፡፡
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በአዋጅ ቁጥር 780/2005 በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ/ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና መቆጣጠር መረጃ የመሰብሰብ፣ መተንተንና ማሰራጨት ሀላፊነት ያለው ተቋም ነው። በተጨማሪም አገልግሎቱ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ የኦፕሬሽን ስራዎን የማከናወን ስልጣን ተሰጥቶታል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሬያ ቤት በኣዋጅ ቁጥር 982/2008 መሰረት የፌደራል መንግስት ገንዘብና ንብረት በወጡት ህጎችና ደንቦች መሰረት መሰብሰቡን፤ መጠበቁንና በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ እና የደረሰበትን ውጤት ለምክር ቤቱ ሪፖርት ለማቅረብ፤ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ላይ የፋይናንስ የክዋኔ፤ የአካባቢ ጥበቃ፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፤ የቁጥጥር ኦዲቶች፤ ልዩ ኦዲቶች እና ሌሎች ኦዲቶችን ለማካሄድ የተቋቋመ መ/ቤት ነው፡፡
0 Comments