የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና በመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን መካከል በትብብር እና በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም ተፈረመ።
በሁለቱ ተቋማት መካከል የመግባቢያ ስምምነቱ የተዘጋጀው ከመንግስት ግዥና ንብረት ጋር በተያየዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል እና የመንግስት ግዢና አስተዳደር በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተጋላጭ እንዳይሆን ተቋማቱ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት መረጃዎችን በመለዋወጥ በጋራ ለመስራት እንዲችሉ ነው።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በወቅቱ እንደተናገሩት አገልግሎቱ በሀገር ደረጃ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰጠውን ተልእኮ ብቻውን ማሳካት ስለማይችል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸው ከመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ የግዥ መረጃዎች ሲኖሩ ተቋማቱ በህጉ መሰረት እንደ ተሰጣቸው ስልጣን ወንጀሎቹን ለመመርመር እንደዚሁም የመንግስት ግዢና አስተዳደር በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ምንጭ እንዳይሆኑ በጋራ መስራት ስለሚያስፈልግ ስምምነቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ በበኩላቸው እንደተናገሩት ከሀገሪቱ አጠቃላይ በጀት ውስጥ ስልሳ አምስት በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ለግዢ የሚመደብ መሆኑን ገልጸው ተቋማቸው የመንግስት ግዢና አስተዳደር በትክክል ስለመከናወኑ ወይም አሰራሩ በትክክል ስላለመፈፀሙ ጥቆማ ሲቀርብለት ኦዲት ማድረግ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ተቋማቸው በሚያከናውነው የኦዲት ተግባር የመንግስት ግዢና አስተዳደር ስርዓቱ ለሙስና እና ለሌሎች የፋይናንስ ወንጀሎች ተጋላጭ እንዳይሆን የሚያከናውነው ተግባር ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ጋር የሚቀራረብ በመሆኑ ወንጀሉን ከምንጩ ለማድረቅ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 649/2001 ማናቸውም የመንግስት መስሪያ ቤት ወይም አቅራቢ ሕግ ከሚያዘው ውጪ ስለመፈጸሙ፤ ግዥ በትክክል ስላለመከናወኑ፤ የግዥውን አሰራር በትክክል ስላለመፈጸሙ ወይም ስለመመሳጠር ጥቆማ ሲቀርብለት ከግዢው አፈጻጸም ጋር የተያያዙ መረጃዎች፤ ሰነዶች፤ መዝገቦች እና ሪፖርቶች እንዲቀርቡለት የማዘዝ እንዲሁም በመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አፈጻጸም ላይ በራሱ ፕሮግራም ወይም በሚደርሰው ጥቆማ መነሻነት ኦዲት ማካሄድ ወይም እንዲካሄድ የማድረግ ስልጣን ያለው ተቋም ነው።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በአዋጅ ቁጥር 780/2005 በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ/ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና መቆጣጠር መረጃ የመሰብሰብ፣ መተንተንና ማሰራጨት ሀላፊነት ያለው ተቋም ነው። በተጨማሪም አገልግሎቱ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ የኦፕሬሽን ስራዎን የማከናወን ስልጣን ተሰጥቶታል።
0 Comments